Depreciation on Buildings Used Partially for Business - Regulation 410/2009
አንድን ሕንፃ ለንግድና ለመኖሪያነት በጋራ ሲጠቀሙ የእርጅና ቅናሽ (Depreciation) እንዴት ይሰላል? የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 አንቀጽ 40ን መሠረት ያደረገ ሙያዊ ትንታኔና ተግባራዊ ምሳሌዎች ለመዳሰስ ሞክረናል መልካም ንባብ።
በከፊል ለንግድ ሥራ የሚውሉ ሕንፃዎች የእርጅና ቅናሽ አያያዝ
በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ብዙ ጊዜ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች አንድን ሕንፃ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ለምሳሌ፦ የታችኛው ክፍል ለሱቅ ወይም ለቢሮ፣ የላይኛው ክፍል ደግሞ ለመኖሪያነት ሊውል ይችላል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች የሕንፃውን የእርጅና ቅናሽ (Depreciation) ለገቢ ግብር ስሌት እንዴት ማቅረብ እንዳለብን ግልጽ መመሪያ ማወቅ ለንግድ ሥራ ስኬታማነት ወሳኝ ነው።
በዚህ ጽሁፍ፣ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 983/2008 እና የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 አንቀጽ 40ን መሠረት በማድረግ፣ በከፊል ለንግድ ሥራ የሚውሉ ሕንፃዎች የእርጅና ቅናሽ እንዴት እንደሚሰላና በኦዲት ወቅት ትኩረት የሚሹ ነጥቦችን በዝርዝር እንመለከታለን።
የአዋጁ እና የደንቡ ትስስር (አዋጅ 983/2008 እና ደንብ 410/2009) ስንመለከት
- አዋጁ (አንቀጽ 25): ስለ ንግድ ሥራ ሃብቶች የእርጅና ቅናሽ ጠቅላላ መርሆዎችን ያስቀምጣል። አንድ ንብረት ለንግድ ሥራ ገቢ ማስገኛ እስከዋለ ድረስ የእርጅና ቅናሽ ሊታሰብለት እንደሚገባ ይደነግጋል።
- ደንቡ (አንቀጽ 40): አዋጁ ላይ የተቀመጠውን መርሆ ወደ ተግባር ሲቀይረው፣ ንብረቱ (በተለይ ሕንፃው) ለሁለት አገልግሎት የሚውል ከሆነ እንዴት መከፋፈል እንዳለበት በዝርዝር ያስቀምጣል።
በመሆኑም ሕንፃው በከፊል ለንግድ ሲውል ደንብ ቁጥር 410/2009 አንቀጽ 40ን እና አዋጁን መሰረት በማድረግ የሚከተሉትን ነጥቦች ማስተዋል ያስፈልጋል፡
- የወጪ ክፍፍል (Apportionment): የሕንፃው የግንባታ ወጪ ለሁለት ይከፈላል። የእርጅና ቅናሽ የሚታሰበው ለንግድ ሥራው በዋለው የቦታ ስፋት (Proportionate share) ልክ ብቻ ነው።
- ለገቢ ግብር የሚፈቀድ ወጪ (Deductible Expense): በንግድ ሥራ ገቢ ላይ ተቀናሽ የሚደረገው በንግድ ስራ ድርሻው ላይ የታሰበው የእርጅና ቅናሽ ብቻ ነው። የመኖሪያው ክፍል የእርጅና ቅናሽ እንደ ወጪ አይያዝም።
- ተያያዥ ወጪዎች (Related Costs): የአዋጁ አንቀጽ 27 እንደሚያመለክተው፣ ከሕንፃው ጋር የተያያዙ ሌሎች ወጪዎች (ለምሳሌ የጥገና ወጪ፣ የንብረት ኢንሹራንስ እና የውሃ/መብራት) ልክ እንደ እርጅና ቅናሹ ሁሉ በስፋት ድርሻ ተከፋፍለው ለንግዱ ክፍል ብቻ ተቀናሽ ይደረጋሉ።
ልዩ ትኩረት የሚሹ ነጥቦች
- የመኖሪያ ክፍል ጥቅማ ጥቅም፡ ሕንፃው የድርጅት ሆኖ ለሠራተኛ መኖሪያነት ካገለገለ፣ ይህ እንደ ንግድ ሥራ ሃብት ሊቆጠር ይችላል (ምክንያቱም ለሠራተኛው የሚሰጥ ጥቅማ ጥቅም ተደርጎ ስለሚወሰድ)። ነገር ግን ለባለቤቱ መኖሪያነት የሚውል ከሆነ በደንቡ አንቀጽ 40 መሠረት ተለይቶ መውጣት አለበት።
ባጭሩ፣ ይህ የደንብ ቁጥር 410/2009 አንቀጽ 40 ድንጋጌ፣ በአዋጅ 983/2008 የተፈቀደውን የእርጅና ቅናሽ መብት "ለንግድ ሥራ ከዋለው መጠን" በላይ እንዳይሆን ገደብ የሚያደርግ እና ግልጽነት የሚፈጥር አሰራር ነው።
መጋቢት 28/2018 አም